ዳግም አገርሽቶ ባለው ኮቪድ - 19 እና በመዛመት ላይ በሚገኘው ሉላዊ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ላይ አዲስ ላንግያ ቫይረስ ቻይና ውስጥ ተከስቷል።
በዚህ ወር ሳይንቲስቶች በኒው ኢንግላንድ የሕክምና ጆርናል ጥናታዊ ፅሁፋቸው ላይ እንዳሰፈሩት ላንግያ ቫይረስ ቻይና ውስጥ መከሰቱን አስፍረዋል።
ሆኖም እስካሁን ድረስ በአዲሱ ላንግያ ቫይረስ ሳቢያ የተመዘገበ ሞት የለም። ቫይረሱም ከሰው ወደ ሰው ይተላለፍ አይተላለፍ አልታወቀም።
አንድ የዋይት ሃውስ ሰነድ ሉላዊ የቫይረስ መስፋፋት መጠን እየናረ እንደሚሔድ አመልክቷል።
ከእንሰሳት ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች በሕዝብ ቁጥር እያደገ መሔድ፣ የአየር ንብረት ለውጥና የሰዎች ባህሪይን ለሉላዊ ወረርሽኝ ተዛማችነት በሁነኛ አስባብነትም ጠቅሷል።
***
በደቡብ ኮሪያ መዲና ሶል በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰልፈኞች የደቡብ ኮሪያ መንግሥት በሰሜን ኮሪያና ቻይና ላይ ይዞት ያለውን ውጥረት ፈጣሪ አቋምና ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር የሚያካሒደውን ወታደራዊ የጋራ ጦር ልምምድ እንዲገታ እንፈልጋለን ሲሉ ጥሪ አቀረቡ።
የተቃውሞ ሰልፈኞቹ የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ከዋሽንግተን ጋር ያለውን ወታደራዊ ትብብር አቋርጦ ከፒዮንግ ያንግ ጋር የሰላም ስምምነት ውልና ትብብር እንዲያበጅ ጠይቀዋል።
የተቃውሞ ሰልፉ የተካሔደው ከፕሬዚደንቱ ጽሕፈት ቤት ሁለት ኪሎ ሜትር ተኩል ርቀት ላይ ከሚገኘው ታሪካዊው ናምዳእሙን በር ላይ ነው።
ከተቃውሞ ሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል አንዱ የሆኑት ቾይ ኡን ሲናገሩ፤
"የዩን ሱክ አስተዳደር ስልጣን ከያዘ አንስቶ ደቡብ ኮሪያ በሰሜን ኮሪያና ቻይና ላይ አክራሪ ፖሊሲ ይዛለች። እኛ ዛሬ እዚህ የተገኘነው በኮሪያ ባህረ ሰላጤ ሰላም እንዲሰፍንና ለኮሪያውያን ዕርቅና ትብብር ጥሪ ለማድረግ ነው" ብለዋል።