ወደ ዩኒቨርስቲ ዘልቀው የነርስና አዋላጅነት ኮርስ ለመውሰድ ለሚሹ ተማሪዎች ተነሳሽነቱን የወሰደው የቪክቶሪያ መንግሥት $270 ሚሊየን ዶላርስ መበጀቱን ያስታወቀው ዛሬ እሑድ ኦገስት 28 ነው።
ከአምስት ዓመት በታች ጊዜ ውስጥ በተነደፈው ፕሮግራም መሠረት በ2023 እና 2024 ለተመዘገቡ ተማሪዎች እስከ $16,500 የሚደርስ በነፃ ትምህርት ዕድል ኮርስ ወጪዎቻቸው ይሸፈናሉ።
ተማሪዎች በሶስት ዓመት የትምህርት ጊዜያቸው $9000 የሚያገኙ ሲሆን፤ ለሁለት ዓመታት በቪክቶሪያ የሕዝብ ጤና አገልግሎቶች ውስጥ ተቀጥረው ከሠሩ ቀሪው $7500 የሚከፈላቸው ይሆናል።
እንዲሁም የድኅረ ነርስ ስልጠናቸውን በከፍተኛ ክብካቤ፣ ድንገተኛ፣ የሕፃናትና ካንሰር ክብካቤዎች አካባቢ ለሚወስዱ በሺህዎች ለሚቆጠሩ ተማሪዎች በአማካይ $10,000 ይሰጣል።