‹‹ዘመን ‹ነጠላ> ነው - የህልም ዓለም ጥለት
የሰው የህይወት ማግ - የሚሸመንለት!››
ለሚል የልብ ቃል
ህልም እንዲህ ተዳምጦ - ሰው ይፈለቀቃል፤
.
አጎዛ አነጥፌ
አንድ እግሬን ዘርግቼ
ሌላውን አጥፌ
በራቁት ጭኔ ላይ - ፈትል እፈትላለሁ
ባዘቶ ጥጥ ይዤ - ሰው ጥጥ ነው እላለሁ፤
በቀጭን ጣቶቼ
ጥጤን አሳስቼ
ልቃሚ እጥላለሁ
ከጥጥ ሰውነት ላይ
ጥጥ ፍሬ እለቅማለሁ
እፈለቅቃለሁ፤
መጄን አስጠግቼ
ጥጥ እዳምጣለሁ፤
ከጣት ያመለጠ
ጥጥ ፍሬ አወጣለሁ፤
ልቃሚ እጥላለሁ፤
ሳስቶና ተባዝቶ
በደጋን ተመትቶ
ሲለሰልስ ገላው
ዘመን እያሰላሁ
ቀለም አቀልማለሁ
ማግ አተልቃለሁ፤
ፈትል እፈትላለሁ፤
ስስ ጥጥ እንደ ገመድ
እጠቀልላለሁ፤
ይህ ጠቢብ ሸማኔ፤
አዳወረው ማጌን - ፈትቶ ጠቀለለው
ከዘሃ አዛመደው - በቀለም ከፈለው፤
ጥለት አጣጥሎ
ግራ ቀኝ ጠቅልሎ
ሰፈረና በክንድ - ለክቶ በጋቱ
ነጠላዬን ሰጠኝ - ሳይዛነፍ ዕለቱ፤
ከጥጥ ነገረ ልብ
ከጠቢብ ሸማኔ
ሀቅ ዳመጥኩና
እውነት ፈተልኩ እኔ፤
//በጥጥና ፈታይ - በሸማኔ እና ዕድሜ - እውነት ሲተነተን//
ህይወት ጥጥ ስትሆን - ህልም ደግሞ ፈታይ
በሰው ሸማኔነት - በዘመን አልጋ ላይ
ሲዳመጥ፣ ሲፈተል - ሲሸመን እሚታይ፤
ታዲያ፤
ከማሳ ተለቅሞ - ጥጥ ከመጣ ወዲያ - ከተፈለቀቀ
ኑባሬውን ለቆ - ክርና ጥለት ጋር - ከተደባለቀ
ሸማኔ ሸምኖት - ከጨረሰው ወዲያ - ካ’ረገው ነጠላ
ምን ተዐምር ቢፈጠር - ቢዘየድ ሺህ መላ
ወደ ጥጥነቱ - ወይ ወደ ልቃቂት - አይችልም ሊመለስ
ተቀይሯልና - ወደ ሌላ ዕቃነት - ከጥጥነት መለስ፤
ይህንን እያየሁ
ከዘመኔ ጥጥ ላይ - ቆሻሻ እለቅማለሁ
ከድሮ መጄ ላይ - ‹ዛሬ› እዳምጣለሁ
‹ትላንት› ይሉት ፀፀት
‹አምና› ይሉት ቁጭት - እፈለቅቃለሁ፤
ይኸው አለሁ አለሁ
‹ቅድም› ይሉት ህመም
በ‹አሁን› ጅማቴ ላይ - ደጋን እመታለሁ፤
ከ‹አምና›ዬ ዳምጬ - ከ‹ድሮ› ፈልቅቄ
በ‹ዛሬ›ው እንዝርቴ - ማጌን አተልቄ
‹ዘመን› አጠንጥኘ - ልቃቂት ለቅቄ
‹ነገ› ይሉት ህልሜን - ላሰራው ነጠላ - ላስሸምነው ኩታ
በጠቢብ ሸማኔ - ድውር አስደውሬው - በቀለም ላስመታ
ይኸው ቋጥሬያለሁ - ማጌን በአገልግሌ - ሸኙኝ መርቃችሁ
ያንን ጥበበኛ - ሸማኔውን ከአገር - አትጣው ብላችሁ፤
ይኸው ሄድኩላችሁ
ዘመኔን እንደ ጥጥ
ህልሜን እንደ ጥለት
ከነገ ክር ጋር - ላስሸምንላችሁ፤
ይኸው እግሬ ወጣ
ከ‹ትላንት› ቀዬ - ከ‹ዛሬ› መሬት ላይ - የቀረኝ ምናለ
ማዶ የሚታየኝ - ሸማኔው ያለበት
‹ነገ› የተሰኘ - ትልቅ አገር አለ፤
ያውና እዚያ ማዶ - የሸማኔው አገር - የሸማኔው መንደር
በል ጥና ጉልበቴ - አቀበቱን ውጣ - ቁልቁለት ተንደርደር
ከ‹ትላንት› ምን ቀረኝ - ለ‹ዛሬ›ስ ምን አለኝ
ህልሜን አስዳውሬ - ‹ነገ›ን አስሸምኘ - አስቋጭቼው ልደር!!
በል ጉልበቴ ጥና፤
በል ተጓዝ እንጓዝ፤
ከ‹ትላንት› ቀዬ - ከ‹ዛሬ› መሬት ላይ - የቀረኝ ምናለ
ማዶ የሚታየኝ - ሸማኔው ያለበት
‹ነገ› የተሰኘ - ትልቅ አገር አለ !!