"ከሎሬየት ፀጋዬ ገብረመድኅን ጋር መሥራት ትምህርት ቤት እንደመግባት የሚቆጠር ነው፤ ሙሉ ሰው ያደርጋል" ተዋናይ ተስፋዬ ገብረሃና

Tesfaye Hamlet.png

Artist Tesfaye Gebrehana. Credit: T.Gebrehana

ተዋናይ፣ ፀሐፌ ተውኔት፣ አዘጋጅና ዳይሬክተር ተስፋዬ ገብረሃና፤ ቀደም ባሉት ሁለት ተከታታይ ክፍለ ዝግጅቶቻችን ከውልደትና ዕድገቱ አንስቶ፣ በኢትዮጵያ የተውኔት ሕይወት መድረክ እንዴት እንዳበበት፤ የግለ ሕይወት ታሪኩን ነቅሶ በምናባዊ ምልሰት አጓጉዞናል። በቀጣዩ ዝግጅት አብቦና ጎምርቶ እንደምን መድረክ ላይ ግዘፍ እንደነሳ ቀንጭቦ ያወጋል።


ጉዞ ተውኔት

ተስፋዬ፤ በ "የውጫሌ ውል" ታሪካዊ ተውኔት ዝናና ሞገስ፤ "በአባትዬው" የማኅበራዊ ሕይወት ትወና ድምቀት ተወስኖ አልቀረም።

ከቶውንም ከተውኔት - ተውኔት፤ ከገፀ ባሕሪይ - ገፀ ባሕሪይ ለዋውጧል።

ሐሙስ፣ ኅምሌት፣ ባለ ካባና ባለ ዳባ፣ መስተዋት፣ የጨረቃ ቤት፣ ውድቅት፣ እርጉም ሐዋሪያ፣ የአመፃ ልጆችና ነፃ ወንጀሎችን በብሔራዊና የሀገር ፍቅር ቲአትር ቤት መድረኮች ተውኗል።

ለተስፋዬ ሀገር ድፍን ኢትዮጵያ ናትና ክፍለ አገራቷን አዳርሷል፤ የጥበብ ማዕዱን አቋድሷል።

ታላቁ የብዕር ዘንገኛ ሎሬየት ፀጋዬ ገብረመድኅን በፑሽኪን አንደበት "መድረክ መቅደስ ነው" እንደሚሉት ሁሉ፤ ለተስፋዬ ታዳሚ የተዋናይ ምስ ነው፤ እስትንፋስ ነው።

ለታዳሚም ተዋናይ የጥበብ ምትሃት ነው፤ እራሱን መድረክ ላይ የሚያይበት መስተዋት።

ያኔ የሀገር ቤት ታዳሚ ከምሳ በኋላ ለሚከፈት የመድረክ መጋረጃ የሚሰለፈው ማልዶ በቁርስ ሰዓት ነው።

ይፈላለጋሉ።

አንደኛው 'መድረክህ ከምን?' ሲል፤ ሌላኛው 'እንሆኝ' ብሎ ሊተውን።

የጥበብ ሰው ሃብቱ ሕዝብ፤ የሕዝብ ቅርሱ ሥነ ጥበብ እንደመሆናቸው።

ለጥበብ ሰው አንዱን የሕይወት መድረክ ከሌላው ማበላለጥ አዋኪ ነው።

"ኅምሌት" ግና ለተስፋዬ ግዝፈት አለው።

በሎሬየት ፀጋዬ ገብረመድኅን የብዕር ፍሰት ከልሳነ እንግልጣር በአማርኛ አንደበት ለመድረክ የበቃ፤ ለተዋናዮቹም የትምህርት ክፍለ ጊዜ ያህል ነበርና።
Tesfaye and Tsegaye.png
Poet Laureate Tsegaye GebreMedhin and Artist Tesfaye Gebrehana (R). Credit: T.Gebrehana
የደመቀባቸው የመድረኩ "የውጫሌ ውል"፣ የቴሌቪዥን ድራማው "ቃል" እና በጥይት እሩምታ ተደናግጦ አንደበቱ የታሰረበት የሀገር ፍቅር ቲአትሩ "መስተዋት" ትውስታዎች ዛሬም ድረስ በአዕምሮ ማኅደሩ ልዩ ሥፍራ ይዘው አሉ።

"ነፃ ወንጀሎች"ን ግና የተውኔት ዓለሙ መሠረት አድርጎ ያነሳል።

በጥበብ በረከትነቱ ብቻ ሳይሆን፤ ለ26 ዓመታት የፍቅር እስትንፋሱ ሆና ካለችው ዝነኛይቱ ድምፃዊት ብፅዓት ስዩም ጋር ሕይወቱ ለትስስሮሽ የበቃውም በ "ነፃ ወንጀለኞች" ተውኔት ጭምር ነውና።
Singer Bitsat Siyoum.png
Singer Bitsat Seyoum. Credit: T.Gebrehana
በቀጣዩ ክፍለ ዝግጅታችን የሚያወጋውም ይህንኑ የፍቅር ሕይወት ጉዞ አስመልክቶ ይሆናል።

Share
Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service