አንኳሮች
- የአዲስ ዓመት መልካም ምኞት
- የኤምባሲ አገልግሎቶች
- ምስጋና
በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው የአዲስ ዓመት እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት።
ለተከበራችሁ በአውስትራሊያ ለምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ - ኢትዮጵያውያን፣
በቅድሚያ እንኳን ለአዲሱ የኢትዮጵያውያን ዓመት 2015 በሰላም አደረሳችሁ።
አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የጤና፣ የዕድገትና የብልፅግና እንዲሆንላችሁ ምኞቴን እገልፃለሁ።
ራሴን ለማስተዋወቅ ፀጋአብ ክበበው እባላለሁ።
በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኜ ተሹሜ በቅርቡ ወደ እዚህ አገር መጥቻለሁ።
ከአንድ ዓመት በፊት በካንቤራ ያለንን ኤምባሲ ዘግተን ወደ አገራችን ተመልሰን ነበር።
ሆኖም፤ ከአውስትራሊያ ጋር ያለን የረጅም ዘመን ወዳጅነትና በርካታ ኢትዮጵያውያን በአውስትራሊያ መኖራቸውን ከግምት በማስገባት ኤምባሲውን ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ ለመክፈት ተወስኖ ሥራ ለመጀመር በእንቅስቃሴ ላይ እንገኛለን።
እንግዲህ፤ ኤምባሲው ሥራ ሲጀምር የምንሰጣቸውን እንቅስቃሴዎች የምናሳውቅ ይሆናል።
በመንግሥት በኩል በርካታ አገልግሎቶች በኦንላይን እንዲሰጡ ተወስኗል።
ይህም አገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍና ጊዜ ቆጣቢ ለማድረግ ታስቦ ነው።
ስለሆነም፤ ኤምባሲው የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ከግምት በማስገባት ለዜጎችና ተገልጋዮች ተደራሽ የሚሆንበትን አድራሻውንና የኮሙኒኬሽን መስመሮቹን በቅርቡ እናሳውቃለን።
በአካል በመምጣትም ሆነ፤ በተለያዩ የኮሙኒኬሽን መንገዶች ልታገኙን እንደምትችሉ ከወዲሁ እናሳውቃለን።
ኤምባሲው ቤታችሁ ነው፤ በሩም ክፍት እንደሆነ እንድታውቁ እንፈልጋለን።
ይኼን ካልኩ በኋላ፤ በአገራችን የሚካሔደውን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታና የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ በመደገፍም ሆነ ከዚህ በፊት በሉዓላዊነታችን ላይ አደጋ በደረሰ ጊዜ ተገቢውን ርብርብ በማድረግ ስላደረጋችሁት ድጋፍ ለማመስገን እወዳለሁ።
አሁንም፤ ስለ ሰላም አስፈላጊነት እንድትናገሩ አበረታታለሁ።
አገራችን ሰላም ያስፈልጋታልና።
ኤምባሲው ቤታችሁ ነው፤ በሩም ክፍት እንደሆነ እንድታውቁ እንፈልጋለን።አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው
ከዚህ ሌላ፤ በተለያየ የቡድን ወይም የብሔር ክፍፍሎች ተከፋፍለን ልዩነቶችን ከማጉላት ይልቅ ኅብረ - ብሔራዊ አንድነታችንን ማጠናከር እንደሚገባን ለማሳሰብ እወዳለሁ።
እንዲሁም፤ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የባሕል አቅሞች በአውስትራሊያ ውስጥ በማስተዋወቅ፤ የአውስትራሊያ ኩባንያዎችና ጎብኚዎች ወደ አገራችን እንዲሔዱ በማስቻል ሁላችንም የአገራችን አምባሳደሮች እንድንሆን አበረታታለሁ።
አገራችን አሁን ከምትታወቅበት ድህነትና ኋላ ቀርነት ወጥታ ወደ ብልፅግና ማምራት እንድትችል ሁላችንም የበኩላችንን እንድንወጣ አሳስባለሁ።
በተለያየ የቡድን ወይም የብሔር ክፍፍሎች ተከፋፍለን ልዩነቶችን ከማጉላት ይልቅ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ማጠናከር እንደሚገባን ለማሳሰብ እወዳለሁ።አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው
በመጨረሻም፤ በቀጣይነት በአንዳንድ የአውስትራሊያ ከተሞች በመሔድ የተወሰናችሁትን እንደማገኛችሁ ተስፋ እያደረግኩ፤ ለአገራችን ዕድገት ሁላችንም በጋራ እንሥራ እላለሁ።
በድጋሚ እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ።
አመሰግናለሁ።