አገረ ኢትዮጵያን ለቅቃ የወጣችው የስፖርት ኮሚሽን ሥራ አስኪያጅ የነበሩትን አባቷን አቶ ፈለቀ ተገኝን እና በትራንስፖርትና ነዳጅ ኩባንያ ውስጥ የአስተዳደርና የሰው ሃብት ሠራተኛ የነበሩትን እናቷን ወ/ሮ ሜሪ ወልደሚካኤልን ተከትላና ታናሽ ወንድሟን አስከትላ ነው።

Selam and her brother.
ከእነ ቤተሰቧ የኢትዮጵያን ምድር ለቅቃ ለስደት ያመራችው ወደ አገረ ኬንያ ነው።
የመዲናይቱ ናይሮቢ የስደት ሕይወት ግና በጽጌረዳ ፍራሽ ላይ የመረማመድ ያህል ማራኪና ምቹ አልነበረም።
ፈታኝና አስቆዛሚ ነበር።
ለሰላም የስደት ፈተናዎች ፈታኝ ብቻ አልነበሩም። የጥንካሬዋ ምንጮችዋም ጭምር ነበሩ።
በለጋ እግሮቿ የአንድ ሰዓት መንገድ እየተጓዘች ባልጠነከሩ እጆችዋ 5 ሊትር ነዳጅ ጨብጣ ለቤተሰቧ ታቀርብ ነበር።
የመንፈስ ሁከትን፤ ከፖሊስ ሽሸጋንም በፅንዓት ተቋቁማ ተወጥታለች።
ለ5 ዓመት 2 ወራት ጉዳይ ያህል ባሳለፈቻቸው የናይሮቢ የስደት ሕይወት ውስጥ የራሷንና የቤተሰቧን ውጣ ውረዶችና ፈተናዎች ብቻ አልተመለከተችም።
የሌሎች ሰዎች ፈተናዎችም ኅሊናዋን ሰቅዞ ይይዛት፤ ልቧን ያደማት ነበር።
እናም ባሕር ማዶ ስትሻገር መብቶቻቸውን ለተነጠቁ ተሟጋች ለመሆን በልጅነት አዕምሮዋ "ሳድግ ጠበቃ ነው የምሆነው" የሚል ዕሳቤ ውስጧ አደረ።
ከናይሮቢ ወደ ፐርዝ
ሰላምና ቤተሰብዋ እ.አ.አ ናይሮቢን ለቅቀው ወደ ምዕራብ አውስትራሊያ ዋና ከተማ ፐርዝ ዘለቁ።

Selam and her family. Credit: SF.Tegegn
ናይሮቢ ሳለች የእንግሊዝኛ ቋንቋን መልመዷ ለአያሌ ስደተኞች ተግዳሮት በሚሆነው የአገሬው ቋንቋ ለመግባባት አልታወከችም።
ሆኖም ከአውስትራሊያ ባሕል ጋር መላመዱ የመናፈሻ ሽርሽር ያህል ቀላል አልነበረም።
ለሰላምና ቤተሰብዋ በመጠኑም ቢሆን ቀደም ብለው ፐርዝ የሠፈሩ አገር አላማጅ የአገር ልጆችን ማግኘታቸው ረድቷቸዋል።
በቀለም ትምህርቷ ለመግፋት ወደ ሁለተኛ ደረጃ የዘለቀችው ሰላም ግና ከወጣት ተማሪዎቹ ጋር ፈጥኖ ለመቀላቀል ባሕላዊ ተግዳሮቶቹን መሻገር የዋዛ ሆኖ አላገኘችውም።
የአንጋገር ቅላፄና አለባበስ እንኳ ክፍተት ፈጥረው ተቀባይነትን ለማግኘት መሰናክሎች ነበሩ።

Selam Feleke: High school Credit: SF.Tegegn
የማይታለፍና የማያልፍ ሁነት የለምና ሰላም የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቀቀች።
ናይሮቢ በልጅነት ትልሟ የወጠነችውን የሰብዓዊ መብቶች የሕግ ባለሙያ ሕልም ዕውን ለማድረግ ከጀለች።
አገርን ለመለወጥ፤ እኛ መለወጥ አለብን።ሰላም ፈለቀ ተገኝ
ሆኖም በቤተሰብ ምክረ ሃሳብ ለጋሽነት ከሕግ ወደ ጤና ትምህርት ፊቷን አዞረች።
በነርስነት ሙያ የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኝታ ተመረቀች።

Selam Feleke Tegegn: Graduation Credit: SF.Tegegn
በእናቴ ኤርትራዊት፣ በአባቴ ኢትዮጵያዊ ነኝ። ሁላችንም አዝነናል። ተበታትነናል። አንድ ስንሆን ፍቅራችን ሌላውንም ይቀይራል።ሰላም ፈለቀ ተገኝ

Selam Feleke Tegegn (L), Feleke Tegegn and Selam Feleke (R). Credit: Kool Life and SF.Tegegn